ደብረ ወርቅ

በከተማዋ የምትገኘው የደ/ወርቅ ማሪያም ገዳም ቤተክርስትያን ከከተማዋ በስተ ምስራቅ አቅጣጫ በተለምዶ አባ ሰላማ እየተባለ ከሚጠራዉ አካባቢ ከፍ ብሎ ከሚታየዉ ቦታ ላይ ያለች ሲሆን ፡- ገዳሟ በ351 ዓ.ም በአስፍሐ ወአፅብሃ ተመሰረተች፡፡ከዚህም ጊዜ ጀምሮ መስዋዕተ ኦሪት ይሰዋባት እንደነበር አባቶች ያስረዳሉ፡፡ ገዳሟ ከተሰራች ከ506 ዓመት በኋላ በ857 ዓ.ም በዮዲት ጉዲት ተቃጠለች፡፡ከዚህም በኋላ በ1372 ዓ.ም በቀዳማዊ ዳዊት በድጋሜ ተሰርታ አገልግሎት እየሰጠች ከቆየች በኋላ በ1533 ዓ.ም በአፄ ገላዉዲዎስ እንደገና ለአሁኑ ትዉልድ የደረሰዉ የመቅደሷ ህንፃ በኖራ ታደሰ፡፡ በአጠቃላይ ገዳሟ ከ250 እስከ 351 ዓ.ም በኦሪት ከዚያም እስከ አሁን ድረስ ክርስትናን ተቀብላ አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች፡፡ በውስጧ በርካታ ቅርሶች ያላት ሲሆን ለአብነት፡-ወንጌላዊ ቅዱስ ሉቋስ የሳላት ወይኑት የምትባል የእመቤታችን ስዕል፡፡ ከወርቅና ከአልማዝ የተሰራ የአፄ ዮሃንስ ዘውድና የነገስታት ልዩ ልዩ ዘዉዶች፡፡ ከወርቅና ከብር የተሰሩ የእጅና የመፆር መስቀሎች፡፡ የአባ ሰርፀ ጴጥሮስ ቆብ፣ መቋምያ፣ የብረት ልብስና መስቀል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ባለቤት የነበሩት ወ/ሮ አበሻ ያበረከቱት የተለያየ የብርና የወርቅ ጉብጉባት ካባዎች፡፡ መስዋዕተ ኦሪት የሚሰዋበት እንደ መቅረዝ፣ ሰንና ብርት ያሉ ቅርሶች፣ የተለያዩ ጥንታዊ የብራና ጽሁፎች ወዘተ፡፡ ከነዚህም ቅርሶች መካከል ከየዓይነቱ በደ/ወርቅ ማርያም ዘመናዊ ሙዚየም በማስገባት ለማንኛዉም የሃገር ዉስጥና የሃገር ውጭ ቱሪስቶች ለጉብኝት አመች በማድረግ ለጎብኝዎች የመዝናኛና የጥናትና ምርምር አገልግሎት በመስጠት ለወረዳዉ የቱሪስት ፣ ለቤተ ክርስትያኗ ደግሞ የገቢ ምንጮች ናቸዉ፡፡